ከዝግጅት ክፍላችን
እንኳን ወደ መጀመሪያ እትማችን በደህና መጣችሁ!
እኛ በፋሺስት ኢጣልያ ጨካኝ የወረራ ዘመን ከአገራቸው ተግዘው በኢጣልያና በሌሎች አገሮች ታስረው የነበሩ ኢትዮጵያውያን ተወላጆች ስንሆን የእስረኞቹ ታሪክ ደብዝዞ እየጠፋ መሆኑን በመገንዘብና የደረሰባቸውን እንግልትና የከፈሉትን መስዋዕትነት መዘከር ግዴታ መሆኑን በመረዳት በመተባበር ማሕበር አቋቁመናል።
ይህም ዕድል የተፈጠረው የኛው ዘመዶች ታስረው የነበረበትን አዚናራ ደሴትን ለመጎብኘት በነሐሴ 2017 የተወሰንን የቤተሰብ አባላት ወደዚያው ባቀናንበት ወቅት ነበር። እስር ቤቱን ስንጎበኝ፣ ካላ ሬያሌ በሚገኘው ሆስፒታል ሕንፃ ውስጥ ግርግዳው ላይ የአንዲት ኢትዮጵያዊት ሴት፣ ከአንድ ትንሽ ወንድና አንዲት ትንሽ ሴት ልጅ ጋር የተነሳችው ትልቅ ፎቶግራፍ ተሰቅሎ አየን። ከዚያን ዘመን እስረኞች መካከል ዛሬ በሕይወት ያሉት ያቺ በፎቶግራፉ ላይ የምትገኘው ትንሿ ልጅ፣ የዛሬይቱ የ94 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ብቻ ናቸው።
ይህ ከብዙ አሥርት ዓመታት በኋላ የተደረገ ጉዞ ይህን ታሪክ ሰብስቦ ማቆየት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እጅግ አመላካች የሆነ አጋጣሚ ነበር። ለዚህም ነው ወደየመጣንበት ከተመለስን በኋላ ድርጅት አቋቁመን ይህን ዓላማ ለማሳካት ጥናት ማካሄድ፣ ወገን ማነቃቃትና መደራጀት የጀመርነው። ይህም የመጀመሪያው እትማችን ለዚህ ሁሉ ዘመናት ድምፃቸው ያልተሰማላቸው ወገኖቻችንን ታሪክ ለመንገር ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል።
እኛም በየግዜው ከሌሎች እስረኞች ተወላጆች ጋር በያሉበት ዘላቂ የሆነ ግንኙነት ለመመሥረት እንጥራለን። ይህ ታሪክ ከኛ ጋር የሚያስተሳስራችሁ፣ እንዲሁም ታሪኩና ዓላማው የሚማርካችሁ ሁሉ አብራችሁን እንድትጓዙም እንጋብዛለን። በሕይወት ጉዞ ውስጥ የዚህን ታሪክ ትውስታን ለማጎልበት፣ በማንኛውም ረገድ የምታደርጉት ትብብር ለታለመው እቅድ ትልቅ አስተዋጽዖ ይኖረዋል።
አብረን ሆነን ያለፈውን በማስታወስ ለወደፊቱ ትውልድ የሚሆን ቅርስ እንገነባለን። በዚህ በመጀመሪያው ቅፅ በዚያን ዘመን እስረኛ የነበሩ ሁለት ሰዎች ታሪክ ቀርቧል፣ እንዲሁም አንድ ታሪካዊ ክስተት ተዘግቦ ለንባብ ቀርቧል። በቀጣይ እትሞቻችንም፣ የተለያዩ ሰዎች የሕይወት ታሪክ መዘከሩን እንቀጥላለን።
ተለይተው የቀረቡ ጽሑፎች
ደጃዝማች ግርማቸው ተክለሐዋርያት
ደጃዝማች ግርማቸው ተክለሐዋርያት
ደጃዝማች ግርማቸው ተክለሐዋርያት በ19 ዓመት ዕድሜአቸው ከፈረንሣይ አገር ትምህርታቸውን አጠናቅቀው ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጣልያን አስሮ፣ ከአገራቸው አውጥቶ ከሦስት መቶ በላይ ከሆኑ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር አዚናራ ወስደው አስረዋቸው ከዚያ ደግሞ ወደ ሎንጎቡኮ አዛውረዋቸዋል።
የደጃዝማች ግርማቸው የሕይወት ጉዞ የትጋት፣ የፅናትና የሕዝብ አገልግሎት ታሪክን ያካተተ ነው። ከእስር ከተፈቱ በኋላ የተዋጣላቸው ጸሐፊ ተውኔትና ደራሲ ሆነዋል።
ከዚህም መሃል እንደ እስረኛ በልጅነት የኖሩበትን ሎንጎቡኮን በሮም የኢትዮጵያ አምባሳደር በነበሩበት ጊዜ እንደነፃ ሰው ቤተ ሰባቸውን አስከትለው ለመጎብኘት የሚገርም ዕድልን ያገኙ ሰው ናቸው።
ከአዚናራ እስረኞች መካከል ታሪካቸው በደንብ ተዘግቦ ከተቀመጠው ጥቂት ሰዎች መካከል አንዱ ደጃዝማች ግርማቸው አንዱ ናቸው። ይህም በቅርቡ ለኅትመት በቅቶ ለንባብ ይቅርባል።
ይቀጥላል...
ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ
ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ
ተግዳሮትና ፈተናን ተቋቁመው ረዥም ዕድሜ ኖረው በዘጠናዎቹ ዕድሜ ክልል ከዚሀ ዓለም ድካም ያረፉት ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ ገና ወጣት ሆነው የጥቁር አንበሳ መሥራች አባል ነበሩ። ከዚያም ጣልያኖች ይዘው በእስረኝነት ወደ አዚናራ ከወሰዷቸው በኋላ ለሌሎች እስረኞች ከለላና ድጋፍ በመሆን ይታወቃሉ። ወይዘሮ ስንዱ መምህርት፣ ደራሲ፣ የሴቶች መብት ተሟጋች፣ ፖሊቲከኛና የሌላም ብዙ ሙያ ባለቤት ነበሩ።
ይቀጥላል...
ጥቁር አንበሳ ከሚባሉ ጋር የሚያያዙ አባላት
ጥቁር አንበሳ
ይህ አጠር ያለ ፅሑፍ ስለ ጥቁር አንበሳ ያትታል። ጥቁር አንበሳ ፋሽዝምን ለመታገል በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተደራጀ የመጀመሪያው ቡድን ነው።
ጥቁር አንበሳ የተቋቋመው ኢትዮጵያ ውስጥ በኢጣልያ ወረራ ግዜ ሲሆን፣ የሥነምግባር፣ የአገር ኩራትና የብርታት ተምሳሌት የሆነ ኃይል ነበር። ቡድኑ ዕድሜው አጭር ቢሆንምና አባላቱ ብዙ ባይሆኑም እንኳ፣ ቅኝ ገዥዎችንና ጭቆናን ለመገዳደር ያደረጉት ተጋድሎ በኢትዮጵያም ለቀጣዩ ትውልድ፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ መድረክ ለሌሎች ታጋዮች አስተማሪ ለመሆን በቅቷል። የጥቁር አንበሳ ታሪክ እነሆ።
ይቀጥላል...
ሰሞነኛ ሁነቶች
የ AAIS ስብሰባ
በመጭው የኢጣልያ ጥናት በአሜሪካ ማሕበር ስብሰባ ላይ ተገኝተን ድርጅታችንን ለማስተዋወቅ ባገኘነው ዕድል መሠረት ይህንን ጥናታዊ ስብሰባ ለመካፈል ዝግጅት ላይ እንገናኛለን። ስብሰባው የሚካሄደው ሳሳሪ ሳርዴኛ፣ ኢጣልያ ከሰኔ 3–5 2018 ድረስ ነው። በዚህ ስብሰባ ላይ የፓነል ውይይት የሚሳተፉ ተወካዮች ይኖሩናል።
የገንዘብ ማሰባሰብ ሂደት
ከዚህ ቀደም ተዘጋጅቶ ከነበረው በራሪ በተሻለ መልኩ አስረጂ የሆነ፣ ጥረታችንን ሁሉ በደንብ የሚገልፅና ድርጅቱን በደንብ የሚያስተዋውቅ፣ በፒዲኤፍ ማውረድ የሚቻል እሱን የሚተካ ሰነድ አዘጋጅተን በማጠናቀቅ ላይ እንገኛለን። እንዳለቀም ከድረ-ገፁ በቀላሉ ማግኘት ይቻላል።
ነሐሴ 2018 ሲመጣ አዚናራ ከሄድን ዓመት ይሞላናል። ለዚህም መታሰቢያ በሚሆን መልኩ ዓመት እስኪሞላን ድረስ $20,000 ለመሰብሰብ እንድንረባረብ ባቀረብነው ጥሪ መሠረት እስከ አሁን የተሰበሰበውና ቃል የተገባው ድምር $6,000 ነው።
ዋናው ዓላማችን አዚናራ ደሴት ላይ እዚያ ታስረው የነበሩ ወገኖቻችንን የምናስብበትና የምንዘክርበት ሚዩዚየም ማቆም ነው። አንዳንዶቹ ካምፖ ፋሮ መቃብር ቦታ ላይ ምልክት እንኳ በሌለው መቃብር አርፈዋል። ይህን ለማድረግ በተቻላችሁ መጠን ዓላማችንን እንደምትደግፉ ተስፋ አለን። እባካችሁ የገንዘብ ድጋፍም አድርጉልን። ማንኛውም የገንዘብ ድጋፍ ደረሰኝ የሚሰጥበትና ከግብር ነፃ የሚሆን ነው።
አዲሱ ድረ-ገፃችን! FOM 2.0
አዲሱ FOM 2.0 ብለን የምንጠራው ድረ-ገፃችን መከፈቱን ስንገልፅላችሁ በደስታ ነው። ፒዬር ሀብቴ፣ ኤልፊና ይጥና እጅግ ደክመው ይህንን የተለየ ዲጂታል ጥራትና አቅም ያለውን ድረ-ገፅ በብዙ ወራት ልፋት እዚህ ስላደረሱልን በጣም እናመሰግናቸዋለን። ይህ አዲስ ድረ-ገፅ መዛግብት በውስጡ ለመያዝ ልዩ አቅም እንዲኖረው ሆኖ የተሠራ ነው። ወገኖቻችን ከእስር በፊት፣ ታስረው ሳለና ከተፈቱም በኋላ በአግባቡ ለመሰነድ ስለሚመቸን፣ ከዓላማችን ጋር እጅጉን የተጣጣመ ነው ብለን እናምናለን።
እባክዎ አዲሱን ድረ-ገፅ www.fromobliviontomemory.org ይጎብኙ። እግረ-መንገድዎን አዲስ የነደፍነውን የመገናኛ መንገድም ይፈትሹ!
የምናወጣቸው መረጃዎች የሚያስደስቱዎ ከሆኑ እባክዎ ድጋፍዎን ይስጡን፦
Donate
አስተዋጽዖ አበርካቾቻችን
ይህ በየሦስት ወሩ የሚወጣ ዝግጅት ሲሆን የዛሬው የመጀመሪያው እትም ላይ ለተሳተፉትና ስማቸው ከዚህ በታች ለተጠቀሰው ምስጋናችን የላቀ ነው፦
ለምርምር፣ ለጽሑፍ እና ለዕርማት፦ ጎሕዓለም አሰፋ፣ እጅጋየሁ ደምሴ፣ ይጥና ፍርድይወቅ፣ ብርሃኔ ግርማቸው፣ መቅደስ መስፍን፣ ዋሲ ተስፋ፣ ሊዲያ ተስፋዬ፤ ያድዋ የወንድወሰን እና ዳግማዊ ይመር።
ለትርጉም፦ ደብሪቱ መርዕድ ካምፖሬያሊ፣ ጋብሪኤላ ጌርማንዲ፣ ኃይሌ ከበደ፣ ቆንጂት ሥዩም።
ለፎቶዎችና ምስሎች፦ ኤልፊ ጌታቸው ኑቬሎን፣ እያሱ ቤትዎስ፣ አሉላ ፓንክኸርስት።